በግብርናው ዘርፍ የወተት ምርት ስራ ላይ ተሰማርቶ የአሶሳን ከተማ ወተት እየመገበ የሚገኝ ታታሪ ጎልማሳ

አቶ ሲሳይ አማረ በአሶሳ ከተማ ነዋሪና የመንግስት ሰራተኛ ሲሆን በግብርናው ዘርፍ የወተት ምርት ስራ ላይ ተሰማርቶ የአሶሳን ከተማ ወተት እየመገበ የሚገኝ ታታሪ ጎልማሳ ነው፡፡

“በ2002 ዓ/ም ከሶስት ከጓደኞቼ 7 ሺ ብር ተበድሬ በአንዲት ላም በግሌ መኖሪያ ቤት ግቢ ውስጥ ነው ስራ የጀመርኩት፡፡ ከውስን ዓመታት በኋላ የከብቶቹ ቁጥር ሲጨምር ስራው መስፋት የሚችል መሆኑን ስገነዘብ ከብድር እና ቁጠባ ተቋም 180 ሺ ለመጀመሪያ ጊዜ በግሌ ተበድሬ የስራው ማስፋፊያ ቦታ በመገንባት አጠናክሬ ቀጠልኩ፡፡ ስራውን እያሰፋሁ አንድም ቀን ሳልዘገይ ዕዳውንም ከፍዬ ስጨርስ ከብቶቹ በቁጥር ወደ 20 በማደጋቸው በድጋሜ 250 ሺ ብር ብድር ወስጄ ባለ-ሶስት እግር ተሸከርካሪ (የጭነት ባጃጅ) በመግዛት ስራውንም ይበልጥ አጠናከርኩ፡፡ የስራው መስፋትና እያስመዘገበ ያለው ውጤት አቅም እየሆነኝ ሲመጣ ሰፊ ቦታ ያስፈልግ ስለነበር በሁለተኛ ዙር የወሰድኩትን ብድር ዘግቼው 300 ሺ ብር ተበድሬ በአሶሳ በተለምዶ አየር መንገድ አካባቢ ሰፊ ቦታ ገዝቼ የላሞችንም ቤት ገነባሁ፡፡

በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ ስራውን ከባድ ከሚያደርጉ ሁኔታዎች መካከል መኖ ማመላለስ አንዱ ሲሆን ይህንም በጉልበቴ ከማመላለስ ጀምሮ የአህያ ጋሪ ተከራይቻለሁ….የጭነት ባጃጅ ገዝቻለሁ….አሁን ደግሞ አበዳሪ ተቋሙን አንድ ሚሊዮን ብር ብጠይቀው 800 ሺ የፈቀደልኝ ስለሆነ 3F መኪና ገዚቼ የላሞች መኖ እና የወተት ምርት ማመላለሻ አድርጌ እየተገለገልኩበት ነው፡፡ ይህ ተቋም እኔን ለስኬት ከማብቃቱም ባሻገር የክልሉ ፕሬዚዳንት ክቡር አሻድሊ ሃሰን ከካቢኔያቸው ጋር ስራ ቦታዬ ድረስ ተገኝቶ ሲጎበኙኝ በሌማት ፕሮግራም ዘርፍ የቀደመ የስኬት ተሞክሮዬን እንዳጋራቸው ምክኒያት ሆኖኛል፡፡ ይህ ስራ አሁን በጣም የሰፋ ስለሆነ ማሽን ይፈልጋል፣ የመኖ ማቀነባበሪያ ይፈልጋል፣ ዘመናዊ ማለቢያም የሚፈልግ ስለሆነ ከፍተኛ ገንዘብ የሚፈልግ ነው፡፡

እኔ ከልጅነቴ ጀምሮ የገበሬ ልጅም ስለሆንኩ የእንስሳት ፍቅሩም አለኝ፡፡ ከዚህም ባሻገር በሳይንሱም ዘርፍ በመጀመሪያ ዲግሪ የእንስሳት ህክምና ባለሙያ ነኝ፡፡ በርግጥ የኑሮ ውድነቱ እየከፋ ሲመጣ የዕለት ጉርሴን ለማገዝ ብዬ ከመንግስት ስራ ጎን ለጎን ይህንን ስራ የጀመርኩት ቢሆንም ፍቅሩም ስለነበረኝ ሞያዬን ከውስጣዊ ፍላጎቴ (Passion) ጋር ለማገናኘት ነው የሞከርኩት፡፡ በመንግስት ስራ ህዝቡን እያገለገልኩ ሲሆን እዚህም በግል ስራዬ ደግሞ ከ15 በላይ ሰራተኞች አሉኝ (በስራ ዕድል ፈጠራው ዘርፍ ቀላል አይደለም)፡፡

በአሶሳ ከተማ ውስጥ በተለይም ከ6 ዓመት ወደዚህ ልጅ ያለው ሰው የላሞቼን ወተት ያውቀዋል፡፡ እኔን ጨምሮ በባለሙያ በመታገዝ ጤንነቱ የተጠበቀ፣ በጣም ጥራት ያለው ትኩስ ወተት በቀን ቢያንስ እስከ 100 ሊትር ለገበያ አቀርባለሁ፡፡ ማንም ማግኘትን ባይጠላም ገንዘብ ከማግኘት በላይ የሚያረካኝ ግን ከወተት መሸጫ ሱቆቼ በር ላይ የላሞቼን ወተት የሚጠብቁ የደንበኞቼን ፍላጎት በአግባቡ አስተናግጄ በየቤቱ ያሉት ህፃናት፣ ታማሚዎች፣ ሽማግሌዎች ትኩስ ወተት እንደደረሳቸው ሳስብ ነውና እንደ እኔ ረክቶ የሚኖር ሰው ያለ አይመስለኝም፡፡

የአሁኑ ትውልድ የግብርና ስራ የሚፈራ ይመስለኛል፡፡ ግን ቆርጦ ለገባ የግብርና ስራ ውስጥ ከራስ ተርፎ ለሌሎች መብቃትም አለ፡፡ በቀጣይ እኔ ከብድር እና ቁጠባ ተቋም ጋር ሆኜ ማር እና እንቁላል ስራ እጀምራለሁ፡፡ እስካሁን ባለው መናገር የምፈልገው ከፈጣሪ ቀጥሎ የደረሰልኝ የብድር እና ቁጠባ ተቋም ባለውለታዬ ነውና ላመሰግነው እፈልጋለሁ፡፡”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *