ያልተጠበቀው የሸርቆሌ ቅርንጫፍ የ2014 ዓም አበራታች የስራ አፈፃፀም እና የአመራሩ ሚና!

ያልተጠበቀው የሸርቆሌ ቅርንጫፍ የ2014 ዓም አበራታች የስራ አፈፃፀም እና የአመራሩ ሚና!

“በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብድር እና ቁጠባ ተቋም የሸርቆሌ ቅርንጫፍ አሰራር ቀደም ሲል ከነበረው በአሁኑ ሰዓት “በብዙ ተሻሽሏል፡፡ በአመራር የሚደገፍ ማንኛውም ነገር ውጤታማ እንደሚሆን ስለምናምን እና ቅርንጫፉን መደገፍ ስላለብን የተቋሙን ደንብና መመሪያን ሳንነካ የህዝባችንን ተጠቃሚነትና የተቋሙንም የዕድገት ቀጣይነት ጉዳይ ማዕከል አድርገን በአሁኑ ሰዓት እንደ ወረዳው አመራር ከሰክተር አመራሮችና ባለሙያዎች እንዲሁም ከቅርንጫፉ ጋር በግልፅ መድረኮች እየተነጋገርን በቅንጅት በርካታ ነገሮች አስተካክለናል፡፡ ተቋሙ መንግስታዊ እና ህዝባዊ ተቋም ነው፡፡ እኛ ደግሞ የመንግስት አካልና የህዝብ አገልጋዮች ስለሆንን እንደ አመራር ከእኛ የሚጠበቀውን እያደረግን ነው፡፡ ጥቅሙ ለትውልድ እስከሆነ ድረስ ማህበረሰባችን የማዕድን ምርት ጨምሮ ከየትኛውም ልማት ከሚያገኘው ገቢ መቆጠብ እንዳለበት የትኩረት አቅጣጫ አስቀምጠን አቋም ይዘን በየቀበሌው እና በተጨማሪ ህዝባዊ መድረኮች እየሰራን ነው፡፡ ከግለሰቦችን በተጨማሪ ተቋማት በተለይም እንደ ማዘጋጃ፣ ገንዘብና ኢኮኖሚ፣ የስፖርት ምክር-ቤት እና ሌሎች ገቢ ሰብሳቢ የመንግስት ተቋማት የሚያገኙትን ገቢ ሙሉ በሙሉ ከብድር እና ቁጠባ ተቋም ሸርቆሌ ቅርንጫፍ በቁጠባ እንዲያስቀምጡ ተነጋግረን ተግባራዊ እያደረግን ነው፡፡ መንግስት ያደራጃቸው የተለያዩ ማህበራትም ቢሆኑ ሃብት ሲያገኙ ድምር ውጤቱ የህዝብ እና የሃገር እድገት መሆን ስለሚገባው የሚያገኙትን ገንዘብ ከአልባሌ ጥፋት ለመታደግ በአቅራቢያቸው ያለውን የብድር እና ቁጠባ ተቋም ቅርንጫፍን መፍትሄ ማድረግ አለባቸው ብለን እየደገፍን ነው ውጤትም አምጥቷል፡፡ በአንድ ጀንበር ከ2 ሚሊዮን በላይ ቁጠባ ወደ ቅርንጫፉ የገባበትን ሁኔታ አስታውሳለሁ፡፡ የብድር አመላለሱንም በሚመለከት በትኩረት ክትትል ስለምናደርግ ቀደም ሲል የነበሩ የውዝፍ ብድር ችግሮች አሁን ላይ አይታዩም፡፡ የመንግስት ሰራተኞች ብድር በፔይሮል ተቀንሶ በወቅቱ ገቢ እየተደረገ ስለመሆኑ ስለምንከታተል ውዝፍ ውስጥ አይገባም፡፡ ትንሽ የሚያስቸግር የነበረው በየቀበሌው ያለው የገጠር ብድር ቢሆንም እሱንም ቢሆን እንደማኒኛውም የመንግስት ስራ አጀንዳ አድርገን በስምሪት ብድር እንዲመልሱ ግንዛቤ እየፈጠርን አፈፃፀሙንንም የምንከታተለው ስለሆነ እየታረመ ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር ከዚህ በኋላ የሚሰራጩ ብድሮች ውዝፍ ውስጥ እንዳይገቡ ማንኛውም ደንበኛ ብድር ፈልጎ ወደ ቅርንጫፉ ሲመጣ የደንበኛውን ሁኔታ የማጥናት፣ ከዚህ በፊት ያለውን የደንበኝነቱን ሁኔታና ለስራ ያለውን ቁርጠኝነትና ተነሳሽነት ጭምር የማጥናት ስራም ከቅርንጫፉ ጋር እየሰራን ነው፡፡ ምክኒያቱም ብድር የሚሰራጭበት ዋናው ምክኒያት ሰው ሰርቶ ተለውጦበት እንዲመልስ ነው እንጂ እርዳታም አለመሆኑን እንገነዘባለን፡፡ በተረፈ እኛ ከምናስተዳድርበት ወረዳ ስር ያለው የብድር እና ቁጠባ ተቋም የሸርቆሌ ቅርንጫፍ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተለውጦ በክልሉ ካሉት 23 ቅርንጫፎች በተለይም በቁጠባ አሰባሰብ፣ በብድር ስርጭትና አመላለስ እንዲሁም በትርፋማነት ተሸሎ አንደኛ በመውጣት የዓመቱ ተሸላሚ መሆኑን ስንሰማ በጣም ደስ ብሎናል፡፡ ምክኒያቱም አምነንበት ነበር ከልብ የደገፍነው ውጤትም አምጥቷል፡፡ በቀጣይም ድጋፋችንን አጠናክረን የምንቀጥል መሆኑን በዚሁ አጋጣሚ ማሳወቅ እፈልጋለሁ፡፡” አቶ ኡመር መሃመድ(የሸርቆሌ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *