የጠቅላላጉባኤስብሰባጥሪንይመለከታል
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብድርና ቁጠባ አክሲዮን ማኅበር በምዝገባ ቁጥር ሐ-8-81-31922 መሰረት የአክሲዎን ድርሻ በመክፈል አባል መሆናቸው ይታወቃል፡፡
ስለሆነም የአክሲዮን ማኅበሩ ባለ-አክሲዮኖች 3ኛ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ነሐሴ 30/2018 ዓ.ም ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት ጀምሮ የተቋሙ ዋና መስሪያ ቤት በሚገኝበት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በአሶሳ ከተማ በዋና መ/ቤት ህንጸ የመሰብሰቢያ አዳራሽ የሚካሄድ ሲሆን የእለቱ አጀንዳዎች የሚከተሉት ናቸው
- የ3ኛ አስቸኳይ ጉባኤ አጀንዳዎች
- ምልዐተ ጉባኤው መሟላቱን ማረጋገጥና ማጽደቅ
- የጉባኤውን ድምጽ ቆጣሪ መሰየም
- የአክሲዮን ማኅበሩን ካፒታል ማሳድግ
- የአክሲዮን ማኅበሩን የተጠራቀመ ትርፍ ወደ ተከፈለ ካፒታል ማዞር ናቸው፡፡
በመሆኑም የተከበራችሁ የባለ-አክሲዮን ተወካዮች በተጠቀሰው ቀን እና ሰአት ማንነተዎን የሚገልጽ የታደሰ መታወቂያ በመያዝ ጉባኤው ላይ እንዲገኙ፤እርሰዎ ካልቻሉ ህጋዊ ወኪለዎ የውክልና ደብዳቤ እና ማንነቱን የሚገልጽ መታወቂያ በመያዝ እንዲቀርቡ በአክብሮት ተጠርተዋል፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብድር እና ቁጠባ ተቋም ማኔጅመንት፣ የውስጥ ኦዲተሮች እና የዋና መ/ቤት ከፍተኛ ኦፊሰሮች በተቋሙ በብዙሃኑ ቅርንጫፎች እየተተገበረ የሚገኘውን የኮር-ባንኪንግ ቴክኖሎጂ በሁሉም ቅርንጫፎቹ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ስልጠና በመውሰድ ላይ ናቸው። ይህ ቴክኖሎጂ በሁሉም ቅርንጫፎች ተግባራዊ ሲደረግ በተቋሙ የወረቀት ስራዎችን(manual) በማስቀረት የአገልግሎት አሰጣጡን ይበልጥ ቀላል እና ቀልጣፋ በማድረግ የደንበኞችንም እርካታ የሚያሳድግ ሲስተም ነው ተብሎ ይጠበቃል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብድርና ቁጠባ ተቋም ከአሶሳ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር በክልሉ የብድር አመላለስ ሁኔታን አስመልክቶ ያደረገውን የጥናት ውጤት ከባለድርሻ አካላት ጋር ገምግሟል።
በመድረኩ ላይ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብድርና ቁጠባ ተቋም ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አስራት ብዙአየሁ ተቋሙ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን የቁጠባ ባህል በማሻሻል የክልሉን የመልማት አቅም በማሳደግ ረገድ የተሰጠውን ተልዕኮ እየተወጣ ስለመሆኑ አመላክተዋል።
ተቋሙ የአሰራርና የተደራሽነት አድማሱን በማዘመንና በማስፋፋት በ23 ቅርንጫፎቹ እየሰጠ ባለው አገልግሎት አጠቃላይ ሀብቱን ከግማሽ ቢሊየን ብር በላይ ማድረሱን ጠቅሰው ህብረተሰቡም በተቋሙ በመቆጠብና በመገልገል ተጠቃሚ እንዲሆን ጠይቀዋል።
የተቋሙ የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሙሳ አህመድ ተቋሙ ለበርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች የብድር አገልግሎት በመስጠትና የቁጠባ ባህላቸውን በማሳደግ በቅርበት እያገዘ መሆኑን አስረድተዋል።
ባለድርሻ አካላትም ህብረተሰቡን በማስገንዘብና በተለያየ መንገድ የብድር አመላለስ ችግሮች እንዲፈቱ ከተቋሙ ጎን በመቆም የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ አስገንዝበዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎችም በጥናቱ የተቋሙን ደንበኞች የብድር አመላለስ ችግር ለመለየትና ሊወሰዱ የሚገቡ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ለማመላከት የተሄደው እርምጃ ጥሩ መሆኑን ገልጸዋል።
በቀጣይም የተቋሙን አጠቃላይ አሰራሮችና የደንበኞችን ሁኔታ ባገናዘበ ተጨማሪ ጥናቶች ተደረገው የደንበኞችን ተገልጋይነት ማሳደግና የብድር አመላለስ ስርዓቱን ማሻሻል እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
ተቋሙ በተሻለ መንገድ ህብረተሰቡን እያገለገለ የሚገኝ አንጋፋ ተቋም እንደመሆኑ ከዚህም በተሻለ ማደግና መስፋት እንዳለበትም ተሳታፊዎቹ አንስተዋል።
በመድረኩም በቀረበው የጥናት ውጤት መነሻነት ሰፊ ውይይት የተደረገ ሲሆን በቀጣይም የተቋሙን የብድር አመላለስ ችግሮች በመሰረታዊነት መቅረፍ እና የደንበኞችን ግንዛቤ ማሳደግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ምክረ-ሀሳቦች ቀርበውበታል።
ዘገባው የ BGM ነዉ።
አቶ ሲሳይ አማረ በአሶሳ ከተማ ነዋሪና የመንግስት ሰራተኛ ሲሆን በግብርናው ዘርፍ የወተት ምርት ስራ ላይ ተሰማርቶ የአሶሳን ከተማ ወተት እየመገበ የሚገኝ ታታሪ ጎልማሳ ነው፡፡
“በ2002 ዓ/ም ከሶስት ከጓደኞቼ 7 ሺ ብር ተበድሬ በአንዲት ላም በግሌ መኖሪያ ቤት ግቢ ውስጥ ነው ስራ የጀመርኩት፡፡ ከውስን ዓመታት በኋላ የከብቶቹ ቁጥር ሲጨምር ስራው መስፋት የሚችል መሆኑን ስገነዘብ ከብድር እና ቁጠባ ተቋም 180 ሺ ለመጀመሪያ ጊዜ በግሌ ተበድሬ የስራው ማስፋፊያ ቦታ በመገንባት አጠናክሬ ቀጠልኩ፡፡ ስራውን እያሰፋሁ አንድም ቀን ሳልዘገይ ዕዳውንም ከፍዬ ስጨርስ ከብቶቹ በቁጥር ወደ 20 በማደጋቸው በድጋሜ 250 ሺ ብር ብድር ወስጄ ባለ-ሶስት እግር ተሸከርካሪ (የጭነት ባጃጅ) በመግዛት ስራውንም ይበልጥ አጠናከርኩ፡፡ የስራው መስፋትና እያስመዘገበ ያለው ውጤት አቅም እየሆነኝ ሲመጣ ሰፊ ቦታ ያስፈልግ ስለነበር በሁለተኛ ዙር የወሰድኩትን ብድር ዘግቼው 300 ሺ ብር ተበድሬ በአሶሳ በተለምዶ አየር መንገድ አካባቢ ሰፊ ቦታ ገዝቼ የላሞችንም ቤት ገነባሁ፡፡
በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ ስራውን ከባድ ከሚያደርጉ ሁኔታዎች መካከል መኖ ማመላለስ አንዱ ሲሆን ይህንም በጉልበቴ ከማመላለስ ጀምሮ የአህያ ጋሪ ተከራይቻለሁ….የጭነት ባጃጅ ገዝቻለሁ….አሁን ደግሞ አበዳሪ ተቋሙን አንድ ሚሊዮን ብር ብጠይቀው 800 ሺ የፈቀደልኝ ስለሆነ 3F መኪና ገዚቼ የላሞች መኖ እና የወተት ምርት ማመላለሻ አድርጌ እየተገለገልኩበት ነው፡፡ ይህ ተቋም እኔን ለስኬት ከማብቃቱም ባሻገር የክልሉ ፕሬዚዳንት ክቡር አሻድሊ ሃሰን ከካቢኔያቸው ጋር ስራ ቦታዬ ድረስ ተገኝቶ ሲጎበኙኝ በሌማት ፕሮግራም ዘርፍ የቀደመ የስኬት ተሞክሮዬን እንዳጋራቸው ምክኒያት ሆኖኛል፡፡ ይህ ስራ አሁን በጣም የሰፋ ስለሆነ ማሽን ይፈልጋል፣ የመኖ ማቀነባበሪያ ይፈልጋል፣ ዘመናዊ ማለቢያም የሚፈልግ ስለሆነ ከፍተኛ ገንዘብ የሚፈልግ ነው፡፡
እኔ ከልጅነቴ ጀምሮ የገበሬ ልጅም ስለሆንኩ የእንስሳት ፍቅሩም አለኝ፡፡ ከዚህም ባሻገር በሳይንሱም ዘርፍ በመጀመሪያ ዲግሪ የእንስሳት ህክምና ባለሙያ ነኝ፡፡ በርግጥ የኑሮ ውድነቱ እየከፋ ሲመጣ የዕለት ጉርሴን ለማገዝ ብዬ ከመንግስት ስራ ጎን ለጎን ይህንን ስራ የጀመርኩት ቢሆንም ፍቅሩም ስለነበረኝ ሞያዬን ከውስጣዊ ፍላጎቴ (Passion) ጋር ለማገናኘት ነው የሞከርኩት፡፡ በመንግስት ስራ ህዝቡን እያገለገልኩ ሲሆን እዚህም በግል ስራዬ ደግሞ ከ15 በላይ ሰራተኞች አሉኝ (በስራ ዕድል ፈጠራው ዘርፍ ቀላል አይደለም)፡፡
በአሶሳ ከተማ ውስጥ በተለይም ከ6 ዓመት ወደዚህ ልጅ ያለው ሰው የላሞቼን ወተት ያውቀዋል፡፡ እኔን ጨምሮ በባለሙያ በመታገዝ ጤንነቱ የተጠበቀ፣ በጣም ጥራት ያለው ትኩስ ወተት በቀን ቢያንስ እስከ 100 ሊትር ለገበያ አቀርባለሁ፡፡ ማንም ማግኘትን ባይጠላም ገንዘብ ከማግኘት በላይ የሚያረካኝ ግን ከወተት መሸጫ ሱቆቼ በር ላይ የላሞቼን ወተት የሚጠብቁ የደንበኞቼን ፍላጎት በአግባቡ አስተናግጄ በየቤቱ ያሉት ህፃናት፣ ታማሚዎች፣ ሽማግሌዎች ትኩስ ወተት እንደደረሳቸው ሳስብ ነውና እንደ እኔ ረክቶ የሚኖር ሰው ያለ አይመስለኝም፡፡
የአሁኑ ትውልድ የግብርና ስራ የሚፈራ ይመስለኛል፡፡ ግን ቆርጦ ለገባ የግብርና ስራ ውስጥ ከራስ ተርፎ ለሌሎች መብቃትም አለ፡፡ በቀጣይ እኔ ከብድር እና ቁጠባ ተቋም ጋር ሆኜ ማር እና እንቁላል ስራ እጀምራለሁ፡፡ እስካሁን ባለው መናገር የምፈልገው ከፈጣሪ ቀጥሎ የደረሰልኝ የብድር እና ቁጠባ ተቋም ባለውለታዬ ነውና ላመሰግነው እፈልጋለሁ፡፡”