በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መረጃ መሠረት 42 አነስተኛ የብድር እና ቁጠባ ተቋማት በኢትዮጵያ ውስጥ ይገኛሉ። ከነዚህም መካከል በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለበርካታ ዓመታት እየተንቀሳንቀሰ የሚገኘው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብድር እና ቁጠባ ተቋም አንዱ ሲሆን ከዕድመ-ጠገቦቹ መካከል ነው፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብድር እና ቁጠባ ተቋም “የቤኒሻንጉል ጉሙዝ አነስተኛ ብድር አቅራቢ አክሲዮን ማህበር” በሚል ስያሜ በአዋጅ ቁጥር.40/1996እና በተሻሻለው አዋጅ ቁጥር 626/2009በፍቃድ ቁጥር 018በፈረንጆቹ የዘመን አቆጣጠር በ2001 ዓ/ም በክልሉ በተለይም ለደሃው የህብረተሰብ ክፍል ቁጠባ መር የፋይናንስ አገልግሎት ለመስጠት ከብሄራዊ ባንክበተሰጠው ፍቃድ መሰረት በክልሉ መንቀሳቀስ ከጀመረ 22 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡

ተቋሙ በክልሉ ውስጥ ባሉት በአራት ልማት ማህበራት እና በክልሉ መንግስት ባለአክሲዮንነት (በ5 ባለአክሲዮኖች) ከትርፍ ክፍፍል የፀዳ ሆኖ በ2001እ.አ.አ በ300,000.00 ብር መነሻ ካፒታልስድስት ቅርንጫፎችን አደራጅቶ የብድር እና የቁጠባ አገልግሎት እንዲሁም የቢዝነስ ማማከርና ገንዘብ የማስተዳደር አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡

የተቋሙዋናተልዕኮ ለደሃው የህብረተሰብ ክፍል በተመጣጣኝ ወለድብድር በማቅረብ ዜጎችን ከአራጣ አበዳሪዎች ብዝበዛ በማላቀቅ ከሚያገኙት ገቢ የቁጠባ ባህል እንዲዳብር በማድረግ የምግብ ዋስትናቸው እንዲረጋገጥ ማገዝ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት በዓመት ከ376.8 ሚሊዮን ብር ብድር የማሰራጨት እና ከ244.5 ሚሊዮን ብር በላይ ቁጠባ የማሰባሰብ አቅም በመፍጠረ ያለውን አጠቃላይ ሃብት(Asset) ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ (583.57 ሚሊዮን) አድርሷል፡፡ እንደዚሁም ተቋሙ ስራ ሲጀምር 300,000.00 ብር የነበረው ካፒታል በአሁኑ ወቅት 126 ሚሊዮን ብር በላይ ደርሷል፡፡ በ2019 እ.አ.አበተቋሙ የስራ አመራር ቦርድ በፀደቀው የአምስት ዓመታት ስትራቴጂክ ዕቅድ መሰረትም አጠቃላይ በደንበኞች እጅተሰራጭቶ የሚገኝ ብር 280.1ሚሊዮን የነበረውን መነሻ ከ1.1ቢሊዮን ብር በላይ ለማድረስም በትኩረት እየሰራ ነው፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብድር እና ቁጠባ ተቋም(ቤጉብቁተ) በክልሉ ውስጥ ያለውን ተደራሽነት እያሰፋ የሚገኝ ሲሆን ከብሄራዊ ባንኩ የስራ ፈቃድ የተሰጠው ማንኛውም የፋይናንስ ተቋም ቅርንጫፎችን ሲከፍት ያለብሄራዊ ባንኩ ፍቃድ መክፈት እንደሚችልና ከከፈተ በኋላ ግን ማሳወቅ እንዳለበት እንዲሁም ቅርንጫፍ ሲዘጋ ደግሞ በስራ አመራር ቦርዱ አማካኝነት ለብሄራዊ ባንኩ ሳያሳውቅና ዕውቅና ሳያገኛ መዝጋት እንደማይችል የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ደንብ ቁጥር (Directive No.MFI/07/96)በሚደነግገውመሠረት በአሁኑ ሰዓት በክልሉ በአሶሳ፣ በመተከል እና በካማሺ ዲስትሪክቶች ስር የተደራጁ 23 ቅርንጫፎችንና ተጨማሪ ሳታላይት ፅ/ቤቶችን በመክፈት ተደራሽ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡

በዚህም ማንኛውም የፋይናንስ ተቋም ከደንበኞቹ ለሚሰበስበው የፍላጎት እና የጊዜ ገደብ ቁጠባ 7 በመቶ ዓመታዊ ወለድ መክፈል የሚገባው ስለመሆኑ እና ከ7 በመቶ በላይ የመክፈል ፍላጎት ያልተገደበ ስለመሆኑ፤ በተጨማሪም የፋይናንስ ተቋማት ብድር ሲሰጡ የሚያስከፍሉት የወለድ ምጣኔ በየተቋማቱ የስራ አመራር ቦርድ የሚወሰን ስለመሆኑ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ “Intrest rates applicaple to micro finance institutions directive No. MFI/29/2017” በሚደነግገው መሰረት በዝቅተኛ እና መካከለኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ አምራች የህብረተሰብ ክፍሎች የብድርና ዘመናዊ የቁጠባ አገልግሎት በመስጠት ኢኮኖሚያዊ ገቢያቸው እንዲያድግ፣ ኑሯቸው እንዲሻሻል ብሎም ድህነት እንዲቀረፍ የማገዝ ተልዕኮውን ይበልጥ እውን ለማድረግ እየሰራ ይገኛል፡፡

ተቋሙ የፋይናንስ ተቋማትን የመከታተልና የመቆጣጠር ስልጣን በኢትዮጵያ ውስጥ ካለውከኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ በሚሰጠው ተከታታይ መመሪያዎች መሰረት ወቅቱን በሚመጥን እና የተቋሙን ፖሊሲ በማይጥስ መልክ ወቅታዊ የገበያ ሁኔታንና እንደየአካባቢው የሚለያየውን የማህበረሰቡን ፍላጎት ግምት ውስጥ እያስገባ የተለያዩ የአገልግሎትማሻሻያዎችን እያደረገ የሚገኝ ሲሆን የፋይናንስ ተቋማት ለግል ተበዳሪዎች የማበደር ጣሪያ አጠቃላይ የተቋሙን ካፒታል አንድ በመቶ መስጠት እንዲችል፣ ለቡድን ተበዳሪዎች የብድር ጣራ በሚመለከት የፋይናንስ ተቋማት የጠቅላላ ካፒታላቸውን አራት መቶኛ መስጠት እንዲችሉ እንዲሁም የብድር መመለሻ ጊዜ በሚመለከት ከቤት ግዥና ግንባታ ውጪ ላሉት የብድር አገልግሎቶች ከፍተኛው የመመለሻ ጊዜ ከአምስት ዓመት መብለጥ እንደሌለበት “Limit of Loans, Repayment period and Provisioning requirement Directive No.MFI/28/2016 4th replacement” በሚደነግገው መሰረት ቀደም ሲል 500,000.00 የነበረውን ከፍተኛ የብድር ጣሪያ ከአንድ ሚሊዮን በላይ በማድረግ የደንበኞቹን ፍላጎት ለማርካት በመስራት ላይ ይገኛል፡፡

ተቋሙ ከጊዜ ወደ ጊዚ እየተሻሻሉ የመጡ በርከት ያሉ የብድር አገልግሎቶችን የሚያቀርብ ሲሆንበደመወዝ ዋስትና፣ በገጠርና በከተማ በቋሚ ንብረት ዋስትና፣ በመደበኛ ጥቃቅንና አነስተኛ ለተደራጁ፣ለአርሶ አደሮች ለግብርና ግብዓቶች አቅርቦት፣ ለባዮ ጋዝና ሶላር ሃይል ማመንጫ የሚሰጡ ብድሮች ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብድር እና ቁጠባ ተቋም በእነዚህ ዘርፎች ከአካባቢያዊ ሁኔታዎች ጋር እያስታረቀ ብድር ለክልሉ ማህበረሰብ የሚያሰራጭ ሲሆን በብሄራዊ ባንኩ Directive No.MFI/28/2016 4th replacement ድንጋጌ ውስጥ በአንቀፅ 8 ንዑስ አንቀፅ 1 መሰረት ከሚሰራጩ ብድሮች ቢያንስ 97 መቶኛው በብድር ውል ስምምነት ላይ የተቀመጠ የብድር መመለሻ ጊዜ ሰሌዳመሰረት በወቅቱ መመለስ እንደሚገባው የሚደነግግ ሲሆንአንዳንድ ብድሮች መመለስ ከነበረባቸው ጊዜ ለምሳሌ፡- በየወሩ የሚከፈል ሆኖ ሳይከፈል ለአንድ ቀን እንኳን ቢዘገይ ተቋሙ በተቋማዊ “ስታንዳርድ” ጉዳይ ተጠያቂ ነው፡፡ ለዚህም በየትኛውም ደረጃ ብድራቸው ውዝፍውስጥየገባባቸውደንበኞች ለገቡበት ውዝፍ ማስታመሚያ የሚሆን በልኩ በስራ አመራር ቦርዱ በፀደቀ መመሪያ እና ለብሄራዊ ባንኩ በተገለፀ ውሳኔ መሰረት በተቋሙ ይጠየቃሉ፡፡

ተቋሙ እጅግ ወጪ ቆጣቢ በሆነ መልክ አገልግሎቱን ተደራሽ እያደረገ የሚገኝ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት በአጠቃላይ በሁሉም መዋቅሩ 225 በላይ የሚደርሱ ሰራተኞች አሉት፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ቁጥር ከቅርንጫፍ ብዛትና ከክልሉ ህዝብ ቁጥር አንፃር በቂ የሚባል አይደለም፡፡ ለዚህም የመንግስት መዋቅር በተለይም በየደረጃው ያሉ የልማት ተቋማት፣ አስተዳደሮች፣ የሰላምና ፀጥታ አስከባሪ ተቋማት፣ የፍትህ ተቋማት፣ አደራጅ ቢሮዎች ወዘተበክልሉ ምክትል ርዕሰ-መስተዳድር ሰብሳቢነት በግብረ-ሃይል መልክ ከክልል እስከ ቀበሌ ድረስ ተደራጅተውየተቋሙ ደንብና መመሪያ መሰረት በቅርበት ተቋሙን ያግዛሉ፡፡ በዚህም የተቋሙ የብድር ገንዘብ ዋነኛ ምንጭ የሚሰበሰበው ቁጠባ ስለሆነ ዜጎች አንድም ሃብት ንብረታቸውን ከአላስፈላጊ ብክነት በመታደግ ለራሳቸው ህይወት ማሻሻያ በሌላም በኩል የመስራት ዕውቀትና አቅም እያላቸው የገንዘብ እጥረት ያለባቸው ዜጎች የብድር ገንዘብ ምንጭ በመሆን ዜጎች የልማቱ ባለቤትና ተጋሪ እንዲሆኑ ቆጣቢ ዜጎች ያለገደብ እንዲበዙ ከማድረግ አኳያ የመንግስት መዋቅሩ ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ተቋሙ የሚያሰራጨው መደበኛና ኢ-መደበኛ (የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ ብድር) የብድር ገንዘብ በወቅቱ ወደ ተቋሙ ተመልሶ ደንበኞች ካልተፈለገ ዕዳና ወጪ እንዲታደጉ፣ ቀድሞ ባልተመለሰው የብድር ገንዘብ ምክኒያት ተቋሙን የካሽ ዕጥረት ሲያጋጥመው ብድር ፈላጊ ደንበኞችም መጉላላት እንዳይደርስባቸው በተጨማሪም የህዝብ የሆነው ተቋም ‘ስታንዳርዱን’ ከሚፈታተኑ ጉዳዮች እንዲላቀቅ ከማድረግ አኳያም የዚህ ግብረ-ሃይል ሚና እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብድር እና ቁጠባ ተቋም የሚያሰራጨው የገንዘብ ዋነኛው ምንጭ የሚሰበስበው ቁጠባ ነው፡፡ ይህ ቁጠባ የሚሰበሰበው ከመንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ ከተለያዩ ሃይማኖታዊና ሃይማኖታዊ ካልሆኑ ልማታዊ ተቋማት፣ ከማህበራት፣ ከኢንተርፕራይዞች፣ ከግለሰቦች፣ ከተማሪዎች ወዘተረፈ ስለሆነ ይህንን ቁጠባ በማሰባሰብ የዜጎችን የገንዘብ ብክነት በመቆጣጠር የወደፊት ራዕያቸው እንዲሳካ ከማገዝ ጎን ለጎን እያደገ የመጣውን የስራ ባህል እና የግልና የቡድን ብድር ፍላጎት በማሟላት፣ የሚሰራጩ ብድሮች ለደንበኞች አቅም ፈጥረው በወቅቱ እንዲመለሱ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ከውዝፍ ዕዳ እና ከድህነት የተላቀቀ ዜጋ ከመፍጠርም ባሻገር ተቋሙ የክልሉ የገንዘብ ካዝና ለማድረግ እጅ ለእጅ ተያይዘን ተግተን ይበልጥ በጋራ እንድንሰራ የተቋሙ የዘወትር መልዕክት ነው፡፡