(በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብድርና ቁጠባ ተቋም የባምባሲ ቅርንጫፍ ደንበኛ)

“የብድርና ቁጠባ ተቋም ወረቴ ነው፣ በሰው ሃገር ሂዶ ከመቀጥቀጥ ተግቶ ከሰሩ ሃገራችንም ዱባይ ናት” ወ/ሮ ሉባባ ኢብራሂም ሰይድ (በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብድርና ቁጠባ ተቋም የባምባሲ ቅርንጫፍ ደንበኛ)

በደርግ ዘመን የ7ኛ ክፍል ተማሪ የነበሩ፣ የልጆች እናት የሆኑ፣ በምግብ አብሳይነት የሰው ቤት ተቀጣሪ የነበሩ፣ የባልትና ሙያ ያላቸው፣ ልጆች ለማሳደግ 8 ዓመት በረሃ የተንከራተቱ፣ መኪና የመግዛት ህልም ስላላቸው ወደ አረብ ሃገር ሊሄዱ ሂደት ጀምረው በደላላ ቤት ሲንከራተቱ የነበሩ፣ ከ20 ሺ ብር ጀምሮ በተከታታይ ዙሮች እስከ 500 ሺ ብር ብድር በመውሰድ የባምባሲ ቅርንጫፍ የግል ብድር ደንበኛ የነበሩ፣ በባምባሲ ወረዳ መለስተኛ የሆቴል ስራ (በተለይ ምግብ) ላይ የተሰማሩ ታታሪ ሰራተኛ የሆኑ፣ በወር ከፍተኛ ገንዘብ መቆጠብ የቻሉ፣ በ1.3 ሚሊዮን ብር የህዝብ ማመላለሻ አባዱላ የገዙ፣ በ50 ዓመታቸው ማህበራዊ ሚዲያን ጨምሮ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ የሆኑ ብርቱ እማወራ ናቸው፡፡

ወ/ሮ ሉባባ ኢብራሂም ሰይድ ሲናገሩ በ1.3 ሚሊዮን የገዙት መኪና በአሁ ሰዓት ከ2.7 ሚሊዮን ብር በላይ አቅም አለው፡፡ “አባዱላ መኪናዬ ሰባት ወር እንደሰራልኝ 2 ሚሊዮን 7 መቶ ሺ ብር እንድሸጥ ተጠይቄያለሁ፡፡ ግን አልሸጥም ጊዜው አሁን ስላልሆነ፡፡ መሸጥም ካለበት በቅድሚያ መኪናው ሌላ መኪና መውለድ አለበት፡፡ ትልቁ ነገር ደግሞ ይህን 2 ሚሊዮን 7 መቶ ሺ ብር ብድርና ቁጠባ እንደሰጠኝ ነው የምቆጥረው፡፡ ተቋሙ ባያስጀምረኝ ይህ ብር ለእኔ ህልም ነበር፡፡ ወላሂ ይህ ተቋም ወረቴ ነው፡፡ አሳድጎኛል፡፡ ብር ለመበደር ሲያስቡ መጀመሪያ ሰርቶ መቆጠብን የተማርኩት ከእነሱ ነው፡፡ እኔም ህይወቴ እስካለ ድረስ ሰርቼ እንዲያልፍልኝ ነው የምፈልገው፡፡ ከተቋሙ ባለመራቄ እጅግ ተጠቅሜለሁ፡፡ ዘወትር እየሄድኩ ምክር እቀበላለሁ፡፡ ትንሽም ይሁን ትልቅ በየጊዜው እቆጥባለሁ፡፡ ዕዳ የምከፍለውም አንድ ቀን እንኳን ሳላዘገይ ነው፡፡ እኔ በአጋጣሚ በማልኖርበት ጊዜ የብድር መክፈያን ቀን ወር በገባ በ16ኛው ቀን መሆኑን ልጆቼ ያውቁታል፡፡ ይከፍላሉ፡፡

ለብድርና ቁጠባ ተቋም እና ሰራተኞቹ የማመስገኛ ቃላት የለኝም፡፡ እኔ የተሻለ የምለውን ኑሮ እየኖርኩ ከሃብታሞቹ ጋር ዕቁብ እየጣልኩ ነው። ልጆቼ ሲመጡ “የእማ ቤትኮ አረብ ሃገር ነው” ይሉኛል።ስራ ይበዛል ማለታቸው ነው። ብዙ ዕቅድ አለኝ ገና ብዙ ሰሪቼ ፈርሃ ሆኜ መኖር እፈልጋለሁ፡፡”